Amhara ICT Development Agency::Home

This e-mail address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it
እቅድ አፈጻጸም ተገመገመ፡፡
የአብክመ ኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጅ ልማት ኤጀንሲ የ2005 ዓ.ም የዘጠኝ ወራት እቅድ አፈጻጸሙን ገመገመ፡፡ የእቅድ አፈጻጸም ግምገማው የኤጀንሲው አመራሮችና ሰራተኞች በተገኙበት የተካሄደ ሲሆን የዞኖቹን ሪፖርት ያካተተው የዘጠኝ ወሩ አፈጻጸም በኤጀንሲው የእቅድ ዝግጅት፣ ክትትልና ግምገማ ባለሙያ በአቶ ሙሉጌታ ዘለቀ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡ ሚያዚያ 11 ቀን 2005 ዓ.ም ለግማሽ ቀን ያህል በኤጀንሲው የስልጠና ማዕከል በተካሄደው ውይይት ላይ በዘጠኝ ወር ውስጥ የተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት ቀርበዋል፡፡
ከቀረቡት ዋና ዋና ክንውኖች መካከልም በዘጠኝ ወራት ውስጥ በጠቅላላው ለ13218 ወንድ 8069 ሴት 5149 የመሰረታዊ ኮምፒውተር ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ ማሕበረሰቡን የኢኮቴ ተጠቃሚ ለማድረግ በተከናወነው ተግባርም በመንግሥት፣ በማሕበረሰቡና በተለያዩ ድርጅቶች የማሕበረሰብ ሁለገብ መረጃ ማዕከላት ተደራጅተዋል፤ በክልሉ በጠቅላላው የተደራጁ የማሕበረሰብ ሁለገብ መረጃ ማዕከላትም 34 ደርሰዋል፤ 16 አዳዲስ የመረጃ ማዕከላትም በመደራጀት ላይ ናቸው፡፡
በየደረጃዉ የሚፈጠረዉን አቅም በብቃት መጠቀም እንዲቻል እና የጊዜና ሀብት አጠቃቀምን ዉጤታማ ለማድረግ ቀደም ሲል በ118 ወረዳዎች የወረዳኔት መሰረተ ልማት ተዘርግቷል፤ በቅርቡም ለ22 አዳዲስ ወረዳዎችና ለ2 መንግስታዊ ተቋማት በድምሩ ለ24 ተቋማት አገልግሎቱን ለመዘርጋት ቅድመ ዝግጅት በመደረግ ላይ ነው፡፡ የገጠር ቀበሌ ሽቦ አልባ ስልክን በማስፋፋት በኩል በያዝነው አመት የ 677 ቀበሌዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተከላ ስራው ተጀምሯል፡፡

ተሳታፊዎች
በክልል ለሚገኙ 5 ሴክተር መ/ቤቶች ፣ ለሁሉም ዞኖችና ለ 3 ከተማ አስተዳደሮች በድረ ገጽ ልማትና አስተዳደር ዙሪያ የአሰልጣኞች ስልጠና ተሰጧል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ዞኖችም ስልጠና የሰጡ ሲሆን ከነዚህም ዉስጥ ሰ/ጎንደር፣ ሰ/ወሎ፣ ዋግ ኽምራ ብ/አ/ዞን ፣ ደ/ወሎ ዞን አስተዳደር፣ አዊ ብ/አ/ዞን ለወረዳዎች ስልጠና በመስጠት የድረ ገፅ ሽፋንን ለማሳደግ ሰፊ ስራ ሰርቷል፡፡ ኤጄንሲው መሠረታዊ የሥራ ሂደት ለውጥ /BPR/ ጥናት ተግባራዊ ባደረጉ አራት መስሪያ ቤቶች የቢ.ፒ.አር ኦቶሜሽን እንዲሁም በ26 መስሪያ ቤቶች ፖርታል በማስለማት በተግባራዊ እንቅስቃሴ ላይ እንደሚገኝ ተመልክቷል፡፡
በቀረበው የኤጀንሲው የዘጠኝ ወር እቅድ አፈጻጸም ላይ በሪፖርቱ መካተት ይገባቸው ነበር የተባሉ ክንውኖችና ሌሎችም ጥያቄዎች ከሰራተኞች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡ በመጨረሻም የኤጀንሲው ስራ አስኪያጅ አቶ ብነግረው ዋሌ በቀሪው ሩብ አመት በትኩረት መሰራት የሚገባቸውን ተግባራት በዝርዝር ለሰራተኞቹ አቅርበው የጋራ ግንዛቤ ተይዞባቸዋል፡፡
በተጨማሪም ስራ አስኪያጁ የዘጠኝ ወሩ የኤጀንሲው እቅድ አፈጻጸም አበረታች መሆኑን ገልጸው ውይይቱን አጠቃለዋል፡፡
የድረ ገጽ ልማት ስልጠና ተሰጠ፡፡
በምስራቅ ጎጃም ዞን አስተዳደር የኢኮቴ ዋና የስራ ሂደት አዘጋጅነት ከመጋቢት 24-28/2005 ዓ.ም በደብረ ማርቆስ ከተማ የድረ ገጽ ልማት ስልጠና ተሰጠ፡፡ ስልጠናዉ የተሰጠዉ በአብክመ ኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጅ ልማት ኤጀንሲ ባለሙያ በአቶ መላኩ ጥላሁን ሲሆን በስልጠናዉ ከሁሉም የዞኑ ወረዳዎች የተዉጣጡ ወንድ 26 ሴት 7 ድምር 33 ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፤ ከእነዚህ ውስጥ አንድ ከበረኸት ወረዳ እና ሁለት ከክልል ሴክተር መስሪያ ቤቶች የመጡ ሰልጣኞች ይገኙበታል፡፡
ስልጠናዉ ንድፈ ሀሳብና በተግባር የታገዘ ሲሆን አብዛኛዉን ጊዜ የተግባር ስልጠናዉ ወስዷል፡፡ በንድፈ ሃሳብ ስልጠናዉም የድረ ገጽ ምንነት፣ ዓይነቶችና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ተካተዋል፤ በተግባር ስልጠናዉም ሰልጣኞች ድረ ገጽ ለማልማት የሚያስፈልጉ ደረጃዎችንና ቴክኒካል ጉዳዮችን በመለየት ተለማምደዋል፡፡
የስልጠናዉ አሰልጣኝ የኤጀንሲዉ የሲስተም ልማትና አስተዳደር ዋና የስራ ሂደት ተ/ባለቤት አቶ መላኩ ጥላሁን በስልጠናዉ መጀመሪያ ላይ አጠቃላይ የስልጠናዉ አካሄድ ምን እንደሚመስል ለሰልጣኞች ገልፀዋል፡፡ አሰልጣኙ አክለዉም ይህ ስልጠና ከተጠናቀቀ በኋላ የሚጠበቀዉ ዉጤት ሁሉም ሠልጣኞች ለየወረዳቸዉ ድረ ገጽ በማልማትና መረጃን ለሚፈልገዉ ህብረተሰብ ለማድረስ ምቹ መንገድ መፍጠር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡ በመቀጠልም የስልጠናዉን ዋና ይዘት በመጀመር ስለ ድረ ገጽ ምንነት አብራርተዋል፤ በዚህም ድረ ገጽ ማለት መረጃን ተደራሽ ለማድረግ በሚያስችል መልኩ የተደራጁ የፔጆች/ገጾች ስብስብ ነዉ፤ ድረ ገጽን በመጠቀም መረጃን አለማቀፋዊ በሆነ መንገድ ተደራሽ ለማድረግ እንችላለን፡፡ ከእኛ አንፃርም የየመስሪያ ቤታችንን ደንበኞች ለማርካት መረጃዎችን እንዲደርሷቸዉ ማድረግ ይገባል፤ ለዚህም ደግሞ ድረ ገጽ አይነተኛዉ መንገድ ነዉ፤ በተጨማሪም አቶ መላኩ የድረ ገጽ አይነቶችን በመዘርዘር አንድነትና ልዩነታቸዉን አቅርበዋል፡፡

ሰልጣኞች በተግባር ስልጠና ወቅት
ለአምስት ቀናት ያህል በነበረዉ ቆይታ ሰልጣኞች ስልጠናዉን ከወሰዱ በኋላ የየወረዳቸዉን ናሙና ድረ ገጽ አልምተዋል፡፡ ከተለሙ ናሙና ድረ ገጾች መካከልም የበረኸት ወረዳ (ከሰሜን ሸዋ ዞን)፣ የእነማይ ወረዳና የደብረ ማርቆስ ከተማ አስተዳደር ድረ ገጾች ለሰልጣኞች ቀርበዋል፡፡
ስልጠናዉን አስመልክቶ ሰልጣኞች አስተያየታቸዉን የሰጡ ሲሆን ስልጠናዉ ጥሩ ነበር፤ በኢኮቴ ዘርፍ ዕዉቀት ማለት ቢዝነስ ነዉ በመሆኑም አሰልጣኙ ያካፈለን ቢዝነስ በመሆኑ ሊመሰገን ይገባል፤ ስልጠናዉን መሰረት አድርገን የሰራነዉን ናሙና ድረ ገጽ ወደ ፊት አሻሽለን ጥሩ ድረ ገጽ መስራት እንችላለን፤ ዞኑ ይህንን ስልጠና ከኤጀንሲዉ ጋር በመተባበር ማዘጋጀቱ ሊመሰገን ይገባዋል፤ ስልጠናዉ መሰጠቱ ባለሙያዉን ለስራ የሚያነሳሳ ነዉ፤ ኤጀንሲዉም ትኩረት ሰጥቶ ስልጠናውን ከዞኑ ጋር በመሆን መስጠቱ በለዉጥ ሂደት ላይ መሆናችንን የሚያመላክት በመሆኑ ጥሩ እንቅስቃሴ ነዉ፤ ይህ ተጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል፤ በማለት ገንቢ አስተያየቶችን የሰጡ ሲሆን ለስልጠናዉ የተሰጠዉ ጊዜ በቂ ስላልሆነ ወደ ፊት በሚሰጠዉ ተመሳሳይ ስልጠና ላይ በቂ ጊዜ መመደብ ይገባል ብለዋል፡፡

በስልጠና ወቅት ከተለሙ ድረ ገጾች አንዱ ለሰልጣኞች ሲቀርብ
በስልጠናዉ ለተሳተፉ የኢኮቴ ባለሙያዎች ሰርቲፊኬት ከተሰጠ በኋላ ወ/ሮ የሽ ዋሬ የምስራቅ ጎጃም ዞን አስተዳደር ኢኮቴ ዋና የስራ ሂደት አስተባባሪ የማጠቃለያ ንግግር አድርገዋል፡፡ አስተባባሪዋ በንግግራቸዉ ከዚህ በፊት በነበረዉ የስድስት ወር የስራ አፈፃጸም ግምገማ ዞኑ በድረ ገጽ ልማት ስልጠና በኩል ወደ ኋላ ቀርቶ ነበር፤ አሁን ግን ኤጀንሲዉን በጠየቅነው መሰረት ስልጠናዉን የሚሰጥ ባለሙያ ተመድቦልን ለመስጠት በቅተናል፤ አሰልጣኙን በዚህ አጋጣሚ ማመስገን እወዳለሁ፤ ወደ ፊት ስልጠናዉን ተጠቅመን ድረ ገጾችን በማልማት ለጥቅም ማዋል ይገባል በማለት ንግግራቸውን አጠናቀዋል፡፡

ሰልጣኞች ሰርቲፊኬት ሲቀበሉ
የድረ ገጽ ልማት ስልጠና ከዚህ በፊት በኤጀንሲዉ በግንቦት ወር 2004 ዓ.ም ከሁሉም ዞኖች ለተውጣጡ ባለሙያዎች የአሰልጣኞች ስልጠና የተሰጠ ሲሆን በተመሳሳይ ለዋግ ኸምራ ዞን ባለሙያዎችም በዚሁ አሰልጣኝ በህዳር ወር 2005 ዓ.ም መስጠቱ ይታወሳል፡፡
ኤጀንሲው የሙያ ብቃት ማረጋገጫ መስጠት ጀመረ
የአብክመ ኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኤጀንሲ በክልሉ ውስጥ በመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጅ ዘርፍ ለሚሠጡ የንግድ ፈቃዶች የሙያ ብቃት ማረጋገጫ መስጠት ጀመረ፡፡ ከዚህ በፊት በፌዴራል ደረጃ በመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ይሠጥ የነበረው የዘርፉ የሙያ ብቃት ማረጋገጫ አገልግሎቱን ለክልሎች ተደራሽ ለማድረግ ያስችል ዘንድ ክልሎች አገልግሎቱን እንዲሠጡ ሚኒስቴር መ/ቤቱ በሠጠው ውክልና መሠረት ኤጀንሲው ከየካቲት ወር 2005 ዓ/ም ጀምሮ የሙያ ብቃት ማረጋገጫውን በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡
ኤጀንሲው በዘርፉ በጅምላ፣በችርቻሮ እንዲሁም በአገልግሎት የንግድ አይነት ለመሠማራት ፈልገው የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ለሚጠይቁ አገልግሎት ፈላጊዎች ተገቢውን መስፈርት ማሟላታቸውን በማረጋገጥ የሙያ ብቃት ማረጋገጫውን ይሠጣል፡፡ አገልግሎቱ በኤጀንሲው የመንግስት መረጃና መሠረተ ልማት አገልግሎት ዋና የሥራ ሂደት በኩል የሚሠጥ ሲሆን የሙያ ብቃት ማረጋገጫ የሚሠጥባቸው ዘርፎች የሚከተሉት ናቸው፡፡
በጅምላ ንግድ
1. የቴሌኮሙኒኬሽን መሳሪያዎች የጅምላ ንግድ
2. የስልክ፣ የሞባይልና መሠል ቀፎ እና የመገናኛ መሳሪያዎች ጅምላ ንግድ
3. የኮምፒውተር፣ የኮምፒውተር መለዋወጫዎች እና ተዛማጅ ዕቃዎች ጅምላ ንግድ
4. የሶፍትዌር ሽያጭ ጅምላ ንግድ
የችርቻሮ ንግድ
1. የስልክ የሞባይል እና መሠል ቀፎ እና የመገናኛ መሳሪያዎች የችርቻሮ ንግድ
2. የቴሌኮሙኒኬሽን መሳሪያዎች የችርቻሮ ንግድ
3. የሶፍትዌር ሽያጭ የችርቻሮ ንግድ
4. የኮምፒውተር፣ የኮምፒውተር መለዋወጫዎች እና ተዛማጅ ዕቃዎች የችርቻሮ ንግድ
አስመጭ
1. የቴሌኮሙኒኬሽን መሳሪያዎች አስመጭ
2. የስልክ፣ የሞባይልና መሠል ቀፎና የመገናኛ መሳሪያዎች አስመጭ
3. የኮምፒውተር ፣ የኮምፒውተር መለዋወጫዎች እና ተገጣጣሚዎች አስመጭ
4. የሶፍትዌር አስመጭ
5. የኮምፒውተር ተዛማጅ ዕቃዎች አስመጭ
ላኪ
1. የቴሌኮሙኒኬሽን መሳሪያዎች ላኪ
2. የስልክ፣ የሞባይልና መሠል ቀፎ እና የመገናኛ መሳሪያዎች ላኪ
3. የኮምፒውተር ፣ የኮምፒውተር መለዋወጫዎች እና ተገጣጣሚዎች ላኪ
4. የኮምፒውተር ተዛማጅ ዕቃዎች ላኪ
አገልግሎት
1. ከብሔራዊ የፖስታ አገልግሎት ውጭ የፈጣን መልዕክት አገልግሎት
2. የቴሌ አገልግሎት
3. የሃርድዌር ማማከር ሥራዎች
4. የሶፍትዌር ማማከርና ማቅረብ
5. መረጃ መቀናበር ሥራዎች
6. መረጃ ቋት ማደራጀት ሥራዎች
7. የቢሮ፣ የሂሳብና የኮምፒውተር ጥገና ሥራዎች
8. የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ የማማከር አገልግሎት
9. ሌሎች የኮምፒውተር ነክ ሥራዎች
10. የኮሙኒኬሽንና የኤለክትሮኒክስ ዕቃዎች ተከላና ጥገና
11. የኢንፎርሜሽንና ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሥልጠና አገልግሎት
አገልግሎት ፈላጊዎች የሰው ሃይል፣ የስራ ቦታ ሁኔታ፣ ማመልከቻና ተያያዥ ሰነዶችን የመሳሰሉ መረጃዎችን በማሟላት ከላይ በተዘረዘሩ ዘርፎች የሙያ ብቃት ማረጋገጫ ከኤጀንሲው ማግኜት ይችላሉ፡፡
ዝርዝር መመሪያዉን ይመልከቱ